Twitter Like

Jan 28, 2013

አሰልጣኙ “ውጤቱን በፍጹም ያልጠበቅነው ነበር ከዛምቢያ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ በቡርኪና ፋሶው እንደግመዋለን ብለን አስበን ነበር” በማለት ከአርብ ምሽቱ የቡርኪና ፋሶ ጨዋታ በኋላ ተናግረዋል። ዋልያዎቹ በወረቀት ላይ በሚሰራ ሂሳባው ስሌት አሁንም ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድል ያላቸው ሲሆን ፥ አሰልጣኝ ሰውነትም “ ለመከላከል ወደ ሜዳ አንገባም ምክንያቱም የምናገኘው አንድ ነጥብ ነውና ፤ ስለዚህ ከናይጀሪያ ጋር በምናደርገው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ጎሎችን ለማሰቆጠር እንጫወታለ”ን ነው ያሉት። አሰልጣኙ አክለውም “ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ካገኘን የነጥብ ድምራችንን አራት በማድረስ ወደ ቀጣዩ ዙር ልናልፍ እንችላለን” ብለዋል። “ከናይጀሪያ ጋር በምናደርገው ጨዋታ አንድ ወይም ሁለት ሳይሆን በርካታ ጎሎችን ማስቆጠር ይገባናል” ሲሉ ስለጨዋታው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በተያያዘ ዜና አሰልጣኙ በቡርኪና ፋሶው ጨዋታ የመስመር አማካዩ የሱፍ ሳላህንና ዳዊት እስጢፋኖስ ፥ በመከላከሉ በኩል ክፍተት ስላለባቸው በጨዋታው እንዳልተጠቀሙባቸው ገልጸዋል። በጉዳት ምክንያት ጨዋታውን አቋርጠው የወጡት አዳነ ግርማ እና አስራት መገርሳ ፥ ተከታታይ ህክምናዎች እየተደረገላቸው ሲሆን ፤ በናይጀሪያው ጨዋታው መሰለፍና አለመሰለፋቸው እስካሁን እንዳልተረጋገጠም የቡድኑ ወጌሻ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባረፈበት ሆቴል የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቶ ወደ በረስተንበርግ ከተማ አቅንቷል። ኢትዮጵያ ከናይጀሪያ ጋር የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታዋን በረስተንበርግ በመጭው ማክሰኞ ምሽት ታደርጋለች። ኢትዮጵያ ናይጀሪያን ማሸነፍና በአንጻሩ ቡርኪና ፋሶ ከዛምቢያ አቻ መለያየት ወይም ማሸነፍ ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፋታል። በሌላ በኩል ለቡድኑ ተጫዋቾች ከማክሰኞው ጨዋታ በፊት በቂ የስነ ልቦና ጥንካሬን ለመፍጠር ከዛሬ ጀምሮ ስራዎች እንደሚሰሩ ከስፍራው የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

0 comments:

Post a Comment