Twitter Like

Feb 4, 2013


ቁንጅና እንደ አንድ ማኅበረሰብ ወግ፣ ባህልና ማኅበረሰባዊ እይታ ወይም አጠቃላይ የማንነት ይትበሃል የራሱ የሆነ ምልከታ እንዳለው ይነገራል፡፡

አንድ ማኅበረሰብ ለቁንጅና የሚኖረው ምልከታ እንዳለ ሁሉ ግለሰብም የራሱ ምልከታ ይኖረዋል፡፡ ለሠዓሊ ዘርዓዳዊት አባተ ቁንጅና ከታሪክ፣ ከማንነትና ከጀግንነት ጋር በተያያዘ እንደሚገለጽለት በሥዕሎቹ ላይ በግልጽ መመልከት ይቻላል፡፡ በብሔራዊ ሙዚየም ባሰናዳው የሥዕል ዐውደ ርዕይ ሠዓሊው ቁንጅናን በግል ዕይታውና የሕይወት ፍልስፍናው ሲገልጸው ይስተዋላል፡፡ ‹‹ቆንጆዎቹ›› የሚል መጠሪያ በሰጠው በዚህ ዐውደ ርዕይ በርካታ ሥራዎቹን ለዕይታ ያቀረበ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ሥዕል ላይም የራሱን ነፃ ሐሳብ ለመግለጽ ሞክሯል፡፡ እንደነ አሉላ አባ ነጋ፣ አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም፣ ዘርዓይ ደረስን የመሳሰሉት አገር አፍቃሪ ጀግኖች በአንድ በኩል፣ የንግሥተ ሳባ፣ የህንደኬንና የሌሎችንም በሴትነታቸው ያልተገደበ ተፈጥሮአቸውንና የሕይወት ስንክሳራቸውን በብሩሹ ዳግም ነፍስ ዘርቶ አሳይቷል፡፡


‹‹ለእነዚህ ጀግኖችና አገር ወዳድ ልባሞች ያለኝ ክብር እየዋለ እያደረ የሚጠነክር ነው፤›› የሚለው ሠዓሊ በብሩሹ ብቻ ሳይሆን በብዕሩም ውዳሴውን አብሮ ያቀርብላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ዘርዓ ያዕቆብ ያሉ የተለየ አስተሳሰብ አራማጆችንም ራሱ በመሰለው መንገድ ገጽታቸውን ገንብቶና በብሩሹ አሽሞንሙኖ ያቀረበ ሲሆን፣ መንፈሰ ጠንካራነታቸውንም የሚገልጽ አቀባብና አቀራረጽ ተጠቅሟል፡፡


በሥዕሎቹ ዐውደ ርዕይ ላይ በልዩነት ከሚታዩ ቁም ነገሮች አንዱ ባህላዊ (መንፈሳዊ) እሴቶች የምንላቸውን የማኅበረሰባችን መገለጫ የሆኑ አስተሳሰቦችና ብሂሎችን በራሱ መንገድ የገለጸበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ሽለላን ከሃያ በላይ በሆኑ ልዩ ልዩ ስሜቶች ውስጥ ሊያሳይ ጥሯል፡፡ ‹‹ሽለላ ለእኔ በድል ሒደት ውስጥ ብቻ ያለ አይደለም፤›› የሚለው ሠዓሊ ሽለላ በንዴት፣ በለቅሶ፣ በሐዘን፣ በፍቅር፣ በፍርሐትና በመሳሰሉት ስሜቶች ውስጥ ሁሉ አካላዊ ገጽታው ምን ሊመስል እንደሚችል ለማሳየት ጥሯል፡፡


እንደ አብዛኛው የዐውደ ርዕዩ ታዳሚ አስተያየት ሽለላ በተለመደው የጦርነትና የጀግንነት ስሜት ውስጥ ያለውን ገጽታ የማወቅ እንጂ ከዛ ባሻገር በዚህ መንገድ ሲመለከቱት አዲስ ልምድ ነው፡፡ ሽለላ በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ወደ ጦርነት ወይም ፀብ ሊያመራ ሲነሳ ወኔውንና ጀግንነቱን ለማሳየት አልፎም ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ለማስመስከር የሚተውነው አጭር ተውኔት ወይም እንቅስቃሴ እንደሆነ ቢታወቅም ሠዓሊው ከዚህ ባሻገር ተጉዞ ሽለላን ሳናውቀውም ቢሆን በእያንዳንዱ ስሜታችን ውስጥ እንዴት እንደምናንፀባርቀው ሊያሳይ ሞክሯል፡፡ በተለይ የሥዕሎቹን አቀባብና አነዳደፍ ለተመለከተ እውነትም የፍቅር ሽለላ፣ የፍራቻ ሽለላና የሐዘን ሽለላ መኖሩን ሊያስተውል እንደሚችል በአስተያየታቸው የሰጡ ታዳሚዎች አሉ፡፡


እንደ ሠዓሊው አገላለጽ ጥበብ በእንዲህ ዓይነት መልክ (አቅጣጫ) ብቻ ትሂድ የሚል መመርያም ሆነ አመላካች ሁኔታ እንደሌለና ጥበብ ለእያንዳንዱ ጥበበኛ የራሱ የሆነ ነፃነትና ምልከታን የምታጐናጽፍ መሆኗን ያስረዳል፡፡ ‹‹ይህ በመሆኑም ሌላው ሰው ሊስማማውና ሊዋጥለት ባይችል እንኳ ግላዊ አተያይንና ፍልስፍናዬን ጥበብ በሰጠችኝ ነፃነትና ዕድል ሁሉ ከመግለጽ ወደ ኋላ አልልም፤›› ይላል፡፡

0 comments:

Post a Comment